ሁለንተናዊ ስብእና ያላቸው በስነ-ምግባር የታነጹ ብቁ ምሁራንን ለማፍራት የስነ-ተዋልዶ ጤና ስልጠና አይተኬ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም ተማሪዎቹን ከስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች በመታደግ ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ከሃገር በቀሉ ታለንት ዩዝ አሶሴሽን እና በስነ-ዋልዶ ጤና ዙሪያ ከሚሰራው ግብረሰናይ ድርጅት “አይፓስ” ጋር በጋራ ለመስራት ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ከተውጣጡ ተማሪዎች እና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የውይይት መድረኩን የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሲሳይ ሸዋአማረ ተማሪዎች ጤናማ እና ስኬታማ እንዲሆኑ የስነ-ተዋልዶ ጤና ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው ከስልጠናው የሚገኘው ውጤትም በገንዘብ የማይተመን መሆኑን በመጥቀስ የስልጠና አሰጣጥ ሂደቱ በምን መልኩ መሆን እንዳለበት እና ይሆናል ያሉትን አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡

የፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማ ተማሪዎች የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግርን መንስኤ፤ ውጤት እና መፍትሄዎች በመረዳት እና የተግባቦት ክህሎታቸውን በማዳበር በእውቀት ብቻ ሳይሆን በጤናም ብቁ በመሆን የህይወት ግባቸውን እንዲያሳኩ ማስቻል ነው ያሉት የታለንት ዩዝ አሶሴሽን እና የአይፓስ ተወካዮች የአካባቢውን የማህበረሰብ ተወካዮች በማወያየት ፤ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመጠቀም የጤና መረጃ ማስተላለፍ፤ የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ድጋፍና ክትትል በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች እና ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ አሳውቀዋል፡፡ 

ፕሮግራሙ ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምጣቱ ለውጤታቸው ልህቀት ከፍተኛ አስተዋጠፅኦ እንደሚያበረክት የተናገሩት የውይይቱ ተሳታፊ ተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን የሚነበቡ የህትመት ግብአቶች፤ የመረጃ ሰሌዳዎች እና በዩኒቨርሲቲው ፈርጀ ብዙ የመረጃ አውታር መኖር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው ለፕሮግራሙ መሳካት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ዶ/ር ሲሳይ ገልጸው ተማሪዎችም ሃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት  ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

 

Whos is online

We have 91 guests and no members online

Call for Papers

Scroll to top