የሠብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት አሳሰበ፡፡

የአትዮጵያ ሠብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር 17ኛ አመታዊ ኮንፈረንስ ‹‹ሠብሎች ለዘላቂ የምግብ ዋስትና እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ›› በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቴ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለፁት በሠብል ልማት ዘርፍ ያሉ የአመራረት ችግሮችን በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የህብረተሰቡ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የግብርናው ዘርፍ ተመራማሪዎችና የምርምር ማዕከላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋማረ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮችን በማካሄድ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን በተግባር በማረጋገጥ ግብዓቱን ለተጠቃሚው ለማድረስ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአትዮጵያ ሠብል ሣይንስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዴ ተስፋዬ ናቸው፡፡

ዶክተር ክንዴ አክለውም የሙያ ማህበሩ የሠብል ልማትን ለማሳደግና በምግብ ዋስትና ላይ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ለመፈተሽ በየሁለት አመቱ ሃገር-አቀፍ ኮንፈረንስ እንደሚያዘጋጅ ጠቁመው በዘንድሮው 17ኛው ኮንፈረንስ በተለያዩ የሰብል ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ከ90 በላይ ሣይንሳዊ የምርምር ስራዎች እንደቀረቡ ተናግረዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ አለም አቀፍ የሣይንስ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት!!

 

Whos is online

We have 84 guests and no members online

Call for Papers

Scroll to top