• Registration

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በከተማው ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች እና በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የምክክር መድረኩ በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ሴቶች ጉዳይና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ መሠረት አስራት እንደገለፁት የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግርና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር የአንድ ተቋሙ ተግባር ብቻ ባለመሆኑ ችግሮቹን ለመቅረፍና የተሸለ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት ሊሰራ ይገባል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ክሊኒክ የህክምና ባለሙያ አቶ ደረጀ ደሳለኝ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት በሃገራችን አሁን ያለበት ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በአለም አቀፍ ደረጃ 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በሃገራችን የሚገኙ ናቸው፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርትታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ለስነ-ተዋልዶ ጤና ችግርና ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ደረጀ ለዚህም ምክንያት የአቻ ግፊትና ለጓደኞቻቸው ታማኝ ለመሆን መሞከር፣ የመገናኛ ብዙሃን በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ፣ የገንዘብ ማጣት፣ ደስታና መዝናናት እንዲሁም ሌሎች አጋላጭ ባህሪያቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ለችግሮቹ ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎችም ላልተፈለገ እርግዝናና ውርጃ እንዲሁም ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና አባላዘር በሽታ ከመጋላጣቸው በተጨማሪ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል፡፡

በወልቂጤ ከተማ ጤና ፅ/ቤት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምላሽን ማስተባበርና መምራት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቶማስ ዘውዴ በበኩላቸው ፅ/ቤታቸው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የዳሠሣ ጥናት በማከናወን የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችና የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ለመከለከልና ለመቆጣጠር ተከታታይነት ያላቸው የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ቶማስ አክለውም የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ ለማዳን ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ቀጣይነት ያለው ተግባር አንደሚያከናውኑ በመጠቆም በከተማው ተቋርጦ የነበረውን የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ፕሮጀክት ለማስቀጠል ከጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በሠጡት አስተያየት ችግሩ የጋራ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚስተዋሉ የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግር አጋላጭ ሁኔታዎችን ለመቅረፍና ከሞራልና ከግብረ-ገብ ውጭ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመከላከል ትኩረት ሠጥተው በቅንጅት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደርና የጉብሬ ክፍለ-ከተማ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘገባው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ነው!

Copyright © 2019. Wolkite University. Designed by Wolkite University ICT

Login Form

Register