• Registration

 

ሠረታዊ የህብረተሰብ ጤና ለማሻሻልና ጥራቱ የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በእውቀት፣ ክህሎትና ስነ- ምግባር የታነፀ የሠው ሃይል  ከማፍራት በተጨማሪም የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በሳይንስና ምርምር የተደገፉና መሠረታዊ ህይወታቸውን የሚያሻሽል ሥራ መስራት እንዳለባቸው የሀገሪቱ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አሰራር ስርዓት አስቀምጧል፡፡

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ አንድአምላክ ደንድር እንደገለፁት የጤና ባለሙያዎችን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ለማብቃትና ከአዳዲስ የጤና ሙያዊ ማሻሻያዎች ጋር ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለጉራጌ ዞን እና ለአካባቢው የጤና ባለሙያዎች እየተሠጠ ነው ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ኮሌጁ በ2011 የትምህርት ዘመን በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሙያ ስነ-ምግብ ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መጀመሩን የገለፁት አቶ አንድአምላክ ዩኒቨርሲቲው በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሙያ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በ2008 ዓ.ም በሃገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀውን የቅድመ ጥናት የብቃት ፈተና ወስደው 83 በመቶ በማሳለፍ ከተሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎች 3ኛ ደረጃ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡

በኮሌጁ ውስጥ ያሉ 92 የህክምናና ጤና ሳይንስ መምህራን በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራትና ጥራት ያለው መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግና የማማከር እንዲሁም በንፁህ የመጠጥ የውሃ እና በመድሃኒት አቅርቦት ዙሪያ የተጠናከረ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን የኮሌጁ ዲን ገልፀዋል፡፡

የኮሌጁ መምህራን እስካሁን በተለያዩ የጤና ዘርፎች 38 ማህበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በ22 የኮሌጁ መምህራን የተቀረፁ 11 የህብረተሰብን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ላይ መሰረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ አንድአምላክ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የወጣቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና እውቀት ለማሳደግ ተከታታይነት ያለው ስራ እየተሰራ እንደሆነ የገለፁት ዲኑ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የሙያ አቅም ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ፕሮግራም ተቀርፆ ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በ2012 የትምህርት ዘመን ተግባራዊ ለማደረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኮሌጅ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሠር ተክለሚካኤል ገብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል እና በዘርፉ ብቃት ያለው ዜጋ በብዛትና በጥራት ለማፍራት ከሚያከናውነው የመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን የህብረተሰቡ የጤና አጠባበቅ ለመሻሻልና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ስራዎች በተቀናጀ መልኩ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአካባቢ፣ በሃገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ በተለዩና የህብረተሰቡ የጤና ችግሮች በሆኑት በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በአካባቢያዊና ሙያዊ ጤና ጥበቃ፣ በስነ-ምግብና ተመሳሳይ ጤና ነክ እክሎች እንዲሁም በባህላዊና ዘመናዊ የመድሃኒት አመራረትና አጠቃቀም ዙሪያ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ በተጨማሪ የተለያዩ ስትራቴጂዎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ቢቀመጡም በማህበረሰቡ አመለካከት፣ እምነትና የእውቀት ጉድለት እንዲሁም በጤና አገልግሎት ሰጪዎችና በአካባቢያዊ የአየር መለዋወጥ ምክንያት በሚከሰቱ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይም ትኩረት አድርገው የምርምር ስራ እንደሚያከናውኑ አክለው ገልፀዋል፡፡

                                        ዘገባው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ነው!!

Copyright © 2020. Wolkite University. Designed by Wolkite University ICT

Login Form

Register