• Registration

 

የምክክር መድረኩን አስመልክቶ በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የአረም ሳይንስ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው መኮንን እንደገለጹት የመጤና ተዛማች አረሞች በተለይም በParthenium hysterophorus L. አረም ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውሰው በግንዛቤ ማስጨበጫና በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት ከጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ፣ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ፤ ከጤና ቢሮ፤ከትምህርት መምሪያ እና ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ጌታቸው መኮንን ጨምረው እንደገለጹት አደገኛ መጤና ተዛማች አረሞች አዳዲስ አካባቢዎችን በፍጥነት በመውረርና ነባር ብዝሀ ህይወትን በማስወገድ የሚታወቁ ሲሆን ይህም ሂደት አረንጓዴው ወረራ (Green invasion) በመባል እንደሚታወቅ አብራርተዋል ፡፡ በተጨማሪም በሀገራችን የተመዘገቡ መጤና ተዛማች አረሞች ሰላሳ አምስት መሆናቸውን ገልጸው የቅንጨ/የረሀብ አረም (famine weed) አንደኛውና ዋነኛው ሲሆን ይህም አረም ሀገራችንን ብሎም ዞናችንን በስፋት በመውረር ላይ እንደሆነ ገልጸው በጉራጌ ዞን መታየት ከጀመረበት ከ1990 ዓ.ም አካባቢ ጀምሮ ቆላማ አካባቢዎችን በስፋት በማጥቃት አስጊ ደረጃ ላይ ያደረሳቸው ቢሆንም የጥቃቱ ስፋት ይለያይ እንጂ በጠቅላላው በዞኑ የሚገኙ ወረዳና ቀበሌዎቻችን ላይ ወረራ በመፈጸም እንደሚታወቅ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በመነሳት የቅንጨ/የረሀብ/ መጤ አረምን አሁን ባለበት ደረጃ ለማስቆምና ለማስወገድ በህዝብ ተሳትፎ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ካልተሰራ በዞናችን የሚካሄዱ የግብርና ምርትና ምርታማነት ስራዎችን በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት የሚኖረው የስርጭት ስፋት፣ ፍጥነትና ወደፊት ለመከላከል ከአቅም በላይ የሆነ የሰው ኃይል፣ የማቴሪያል አቅርቦትና ወጭን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠይቅ እንዲሆን ስለሚያደርገው የህዝብ፤ የመንግስትና የሚመለከታቸው ተቆርቋሪ አካላት ሁሉ የመከላከልና የማስወገድ ተግባራዊ አቋም እንዲወስዱ ለማድረግ ታስቦ የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ መዘጋጀቱን ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል ፡፡

ስልጠናው በዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ እና ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተውጣጡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን አማካይነት የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው ይዘትም፡-

  • የአረንጓዴው ወረራና የረሃብ አረም በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ፤
  • የረሀብ አረም ስጋትና የቁጥጥር ዘዴዎች በኢትዮጵያ
  • በጉራጌ ዞን የረሀብ አረም በአፈር ስነ-ምህዳር ጤና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ፣
  • የረሀብ አረምና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች ላይ የአርሶ አደሩ ግንዛቤና ጥረት፣
  • የረሀብ አረም በእንስሳት ጤና ምርታማነት ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ
  • የረሀብ አረም በሰው ጤና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ በሚሉ መሰረታዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠናው መሰጠቱን ዶክተር ጌታቸው መኮንን ገልጸዋል፡፡

ከላይ የተገለጹት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በምክክር መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡበት ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች መጤና ተዛማች አረሞችን ለማጥፋት በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ውስጥ ሚናቸውና ሀላፊነታቸው ከፍ ያለ በመሆኑና አረሙን በመቆጣጠርና የማህበረሰቡን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ የሴክተር መስሪያ ቤቶቹ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ ይህንን ከግምት በማስገባት በምክክር መድረኩ እንዲሳተፉ መደረጉን ዶክተር ጌታቸው ገልጸው በተጨማሪም በምክክር ሂደቱም እነዚህ መጤና ተዛማች አረሞች የወረራ መጠናቸው እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን በመለየት ለአብነትም ፓርቲኒየም በሀገራችን ደረጃ ከ2 (ሁለት) ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሸፈነ መሆኑን፤ በተጨማሪም በምስራቅ ጉራጌ አካባቢ ፕሮስፒስ አሁን ላይ በስፋት እየተከሰተ ያለ አረም ሲሆን ይህም ከሀገራችን ከ1(አንድ) ሚሊዮን ሄክታር በላይ እየሸፈነ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው ከዚህም መነሻ እነዚህ አረሞች በጉራጌ ዞን ደረጃ ያላቸው ወረራ እጅግ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በተፈጠረው ግንዛቤ ልክ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ዶክተር ጌታቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ሀገርአቀፋዊና አለማቀፋዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር በተለይም ከኢትዮጵያ መጤና ተዛማች አረሞች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬትና ከሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራትና የተሻሉ ግንኙነቶችን በመፍጠር በጉራጌ ዞን ያሉትን መጤና ተዛማች አረሞች መቆጣጠርና ችግሩን ለማስወገድ ከየሴክተር መስሪያ ቤቱ የተውጣጣ የስራ የድርጊት ቡድን መዋቀሩን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በግንዛቤ ማስጨበጫና በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ክፍሌ ሌንቴሮ ሲሆኑ እሳቸውም በበኩላቸው እንደገለጹት የኒቨርሲቲያችን ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ትኩረት በመስጠት ቢያንስ በአመት ሶስት ጊዜና ከዚያም በላይ የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉና በየሴክተር መስሪያ ቤቱ የተገመገሙ የስልጠና መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ገልጸው ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በሚገባ ከተወጡ ካሰብነው አላማ እንደርሳለንና በብርታትና በየእኔነት ስሜት ለማህበረሰባችንና ለሀገራችን ልንሰራ ያስፈልጋል በማለት ገልጸዋል፡፡

Copyright © 2022. Wolkite University. Designed by Wolkite University ICT

Login Form

Register