• Registration

 

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የተግባራዊ ሳይንስ እና የሀገር በቀል እውቀት ለማህበረሰብ ልማት›› በሚል መሪ-ቃል አመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ እያካሄደ ነው፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በእውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ከማፍራቱ በተጨማሪ የህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ዶክተር ፋሪስ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ መሰረት ያደረገው የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት የተልዕኮና ትኩረት መስክ ልየታ ጥናት መሰረት ከተመደቡት 15 የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በ2022 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚገኙ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ ለመገኘት ርዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት አስተባባሪ ዶክተር መኩሪያ ታደሠ በበኩላቸው ተቋማቸው ሀገር በቀል እውቀት ማመንጨትና ሽግግር፣ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርምር ክህሎትና አቅም ግንባታ፣ የግብርና ልማትና እድገት እንዲሁም የህብረተሰቡ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በዋናነት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተግባራዊ ሳይንስና በሀገር በቀል እውቀት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የማህበረሰቡን ችግር በመለየት የምርምር ስራዎችን እያከናወነና ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋማረ ዩኒቨርሲቲው በተለይም የልህቀት ማዕከል በሆኑት በባዩ-ቴክኖሎጂ እና በሀገር-በቀል እውቀት ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ጉባኤው በዩኒቨርሲቲው ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ሲሳይ በጉባኤው የሚቀርቡት የምርምር ስራዎች ለተቋሙ መምህራን ግብዓት እንደሚሆናቸውና ወደ ማህበረሰቡ ለማውረድ የተሻለ አጋጣሚ እንደሚፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡

በሁለቱ ቀናት ቆይታ ከአራቱም ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የምርምር ተቋማት የሚሳተፉ ምሁራን በአራት ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ ተፈጥሮ ሃብትና አካባቢያዊ ሳይንስ፣ በሠው ልጅ ጤናና በወሳኝ ተያያዥ ጉዳዮች እና በቢዝነስ፣ ሀገር በቀል እውቀትና አስተዳደር እንዲሁም በቴክኖሎጂ፣ ኢንፎርሜሸን እና ኮሙኒኬሽን 49 የጥናታዊ ፅሁፍ ውጤቶች እንደሚያቀርቡ የተገለፀ ሲሆን ተሳታፊዎችም በጉባኤው የተለያየ ልምድና እውቀት እንደሚለዋወጡበትና ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች በቀጣይ ለማከናወን ትልቅ ግብዓት እንደሚያገኙበት ይጠበቃል፡፡

በአመታዊው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ዶክተር መኩሪያ ታደሠ፣ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮናስ ዮሃንስ እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራንና ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

Copyright © 2021. Wolkite University. Designed by Wolkite University ICT

Login Form

Register